የፍትህ ሚኒስቴሩ መልዕክት

የክቡር ፍትህ ሚኒስቴሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ መልዕክት

ፍትህ ሚኒስቴር የሀገራችን የዴሞክራሲና ፍትህ መሰፈን፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲሁም የህዝቡ የላቀ ተጠቃሚነት ያለ ሕግ የበላይነትና የፍትህ ዘርፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊረጋገጥ አይችልም፡፡

የአገራችን የፍትህ ዘርፍ ታሪክ ስር በሰደዱ አናቂ የሕግና የአሰራር እንዲሁም የአመለካካት ችግሮች የተተበተበ እና የጉልበተኞች ምርኮኛ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በተጀመረው አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ተቋማችን የሕግ እና ፍትህ ሪፎርም በማከናወን እንዲሁም የአሰራር ችግሮችን በማሻሻል፣ ከሰብአዊ መብት አኳያ የሕግ ታራሚዎችን አያያዝ በማስተካከል ተቋማዊ አግልግሎትን ቀልጣፋ፣ ፍትሀዊና ውጤታማ የሆኑ የፍትህ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ መሠረታዊ የለውጥ ተግባራትን አከናውኗል፣በማከናወን ላይም ይገኛል፡፡

ፍትህ ሚኒስቴር በአገራዊ የለውጥ ጉዞ ዳር ለማድረስ በሚደረገው ሰፊና ሁለንተናዊ ርብርብ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 በተሰጠው ስልጣን የፍትህ እና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማክበርና ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ፍትህን በማስፈን፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ ሀገራዊ ተልዕኮውን ከመቸውም ጊዜ በላቀ ደረጃ በመወጣት ላይ ነው፡፡

ተቋሙ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ የህዝብና የመንግስት አመኔታ የተቸረው ተቋም በመሆን የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ በማድረግ የተጀመረው የልማት፣ የሰላም፣ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለብት ብሎም የፍትህ ሥርዓትን ግልፅነት፣ ነፃነትና ተጠያቂነት አሰራርን በማሻሻል በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በዘላቂነት ለውጡን ለማፋጠን የነቃና የተጠናከረ የህዝብ እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ከመቸውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋል፡፡ ፍትህ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና መሰረት ነው፡፡

ፍትህ የምክንያታዊነትና የእውነት ማንፀባረቂያ ሲሆን የሕግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር አገራችን በሁሉም መስክ የተለወጠችና የበለጸገች፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ተምሳሌት እንድትሆን ለማድረግ በሚከናውኑ ተግባራት ላይ መላው የአገራችን ህዝብ ከጎናችን በመቆም የሕግ የበላይነትን በማስፈንና ተቋማዊ ለውጡን ለማረጋገጥ በምንሰራው ስራ በባለቤትነት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የለውጡ ፈፃሚና ዋና ተዋናኝ እንድትሆኑ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

አመሰግናለሁ
ለሕግ፣ ለፍትህ፣ ለርትዕ!