የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ተግባር እና ኃላፊነት

የሙስና ወንጀሎች ምንነት እና ባህርይን ግምት ውስጥ በማስገባት በአዋጅ ቁጥር 881/2007 እና በሌሎች አዋጆች የሙስና ወንጀል ተብለው የተዘረዘሩት ጉዳዮችን የሚመለከቱ የወንጀል ምርመራ ስራ የሚመራበት፣ ተገቢውን ህጋዊ ውሳኔ በዐቃቤ ሕግ የሚወሰንበት እንዲሁም በፍርድ ቤት ክርክር የሚደረግበት የስራ ክፍል ነው፡፡

ቀደም ሲል ይህ ተግባር በተለያዩ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የስራ ክፍሎች በተለይም በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተሰበጣጥረው ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ከሙስና ወንጀል ልዩ ባህርይ እና ውስብስብነት እንዲሁም የከፍተኛ አመራሩን ቀጥተኛ ክትትል እና ድጋፍ የሚጠይቅ ስራ መሆኑን እንዲሁም የስራ ቅብብሎሽ ለማስወገድ፣ ከፍርድ ቤት ጋር የተናበበ አደረጃጀት የመኖሩ አስፈላጊነት እንዲሁም የጉዳዮችን አያያዝ ወጥነት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ከግምት በማስገባት የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ክትትል በማዕከል ደረጃ በተቋቋመው በዚህ ዳይሬክቶሬት ስር እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ይህ የስራ ክፍል ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ በስሩ የመንግስት ተቋማት የሙስና ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ማስተባባሪያ ፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች የሙስና ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ማስተባባሪያ እና የህዝባዊ ድርጅቶች የሙስና ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ማስተባባሪያን ይዞ የሚከተለሉት ተግባራት እና ሀላፊነት ይኖሩታል፡፡ 

 1. የተቋሙንና የዘርፉን ዕቅድ መነሻ በማድረግ የስራ ክፍሉን ተግባራት ያቅዳል፣ አፈፃጸማቸውን ይከታተላል ፣ድጋፍ ይሰጣል፤ 
 2. ከስራ ክፍሉ ጋር ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች ለመቅረጽ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባል፣ 
 3. ለስራ ክፍሉ የሚያስፈልገውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ግብአት እንዲሟላ ያደርጋል፣ ስራ ላይ መዋሉን ይከታተላል፣ 
 4. የስራ ክፍሉ ተግባራት የሚመሩበትን መመሪያዎች እንዲዘጋጁ ያደርጋል ፣ሲፀድቁም በአሰራሩ መሠረት መፈጸማቸውን ያረጋግጣል ፣ በየጊዜው እንዲሻሻሉ ሃሳብ ያቀርባል፤ 
 5. በስራ ክፍሉ ያሉ ባለሙያዎችን የክህሎት ክፍተት ለይቶ አቅማቸው የሚገነባበትን ስልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋል፤የስራ ክፍሉን ሰራተኞችን የስራ አፈፃፀም ይመዝናል፤ 
 6. ከዘርፉ ኃላፊ ጋር በመመካከር ለስራ ክፍሉ ተልእኮ መሳካት አስተዋፅኦ ካላቸው ተቋማትና የሥራ ክፍሎች ጋር የሥራ ግንኙነቶችን ይፈጥራል፣ በቅንጅት ይሰራል፤ 
 7. ከስራ ክፍሉ ተልእኮ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ያደራጃል፣ 
 8. ለስራ ክፍሉ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን እና ቅሬታዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል፣ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል፤ 
 9. የስራ ክፍሉን የስራ አፈፃፀም ይከታተላል፣ ይገመግማል፣ ከቡድኖች ሪፖርት ይቀበላል፣ ግብረ መልስ ይሰጣል፣ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዘጋጅቶ በወቅቱ ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፣ 
 10. በስራ ክፍሉ ተልእኮ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የሕዝብ መድረክ ያዘጋጃል፣ያሳትፋል፣ 
 11. የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞች በተቀመጡ እሴቶች መሠረት በስነምግባር እና በባለቤትነት ስሜት እንዲሰሩ እና ውጤታማ እንዲሆኑ የኮቺንግ (Coaching) ሥራ ያከናውናል፣ በስራ ክፍሉ ያሉትን ሰራተኞች በስነምግባር እንዲገነቡ ያደርጋል፣ ጥሰት ሲፈፀም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያደርጋል፤ 

የስራ ክፍሉ ተግባርና ኃላፊነቶች፡- 

ከላይ ከተገለጹ ለተቋሙ ዳይሬክቶሬቶች በወል ከተሰጡ ተግባር እና ኃላፊነቶች በተጨማሪ በሚከተሉት የወንጀል ጉዳዮች ክትትልን አስመልከቶ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ የተሰጡትን ተግባር እና ኃላፊነትን ከዚህ በታች በተዘረዘሩት የወንጀል ጉዳዮች ላይ ይፈጽማል፡፡ 

በስራ ክፍሉ የሚታዩ የወንጀል ጉዳዮች፡- 

የሙስና ወንጀሎችን በተመለከተ የወንጀል ምርመራ እና ክርክር ሂደትን በበላይነት ከመመራት ባሻገር 

 1. በስልጣን አለአግባብ መገልገል፣ 
 2. የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅቶች ስራን በማይመች አኳሃን መምራት፣ 
 3. አደራ የተሰጠው እቃ ያለ አግባብ ማዘዝ፣ 
 4. በስራ ተግባር የሚፈፀሙ የመውሰድና የመሰወር ወንጀል፣ 
 5. በስልጣን ወይም በሃላፊነት መነገድ፣ 
 6. ያለ አግባብ ጉዳይን ማጓተት፣ 
 7. ያለ አግባብ ፈቃድ መስጠት ወይም ማፅደቅ፣ 
 8. የስራ ሚስጥርን መግለፅ፣ 
 9. በሌለው ስልጣን መጠቀም፣ 
 10. በግል ተሰሚነት መነገድ፣ 
 11. ጉቦ መቀበል ወይም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም መስጠት ወይም መቀበል፣ 
 12. አስታራቂ ሽማግሌዎች የሚፈፅሙት ጉቦ መቀበል ወንጀል፣ 
 13. በሙስና ወንጀሎች የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ስለመርዳት፣ 
 14. በህገ ወጥ መንገድ ዋጋ ያለውን ነገር ያለ ክፍያ ወይም ያለበቂ ክፍያ ማግኘት፣ ዋጋ ያለው ነገር ያለ በቂ ክፍያ መስጠት፣ 
 15. ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብና ንብረት ይዞ መገኘት፣ 
 16. ገንዘብ ማቀባበል፣ 
 17. በምርጫ ላይ የሚስጥ መደለያ፣ 
 18. በከባድ አታላይነት የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች፣ 
 19. በከባድ እምነት ማጉደል የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች፣
 20. የመንግስታዊ ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት ወደ ሀሰት መለወጥ፣ ማጥፋት ወይም ጉዳት ማድረስ፣ ወይም በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ሙስና ወንጀሎች፣ 

ከሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ጠቋሚ፣ ምስክር የሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርስ ጥቃትን አስመልክቶ የሚፈጸም ወንጀል የሙስና ወንጀሎችን ምርመራ እና ክስ ከማደናቀፍ ጋር ተያይዞ በአዋጁ ቁጥር 433/97 (አዋጅ ቁጥር 883/07 እንደተሻሻለ) የተደነገጉ ወንጀሎች በልዩ ህጎች የሙስና ወንጀል ተብለው የተደነገጉ ጉዳዮች፣ 

በሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ የስራ ክፍሎች ከሚታዩ ሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ጋር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች በተደራቢነት የሚገኝ በሚሆን ጊዜ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስከትለው ጉዳይ የሙስና ወንጀል ክሱ በሚሆንበት ጊዜ ከላይ በተጠቀሱት የወንጀል ጉዳዮች በፍርድ ቤት የተላለፈ የገንዘብ ቅጣትን በወንጀል ህጉ መሰረት ያስፈጽማል፣ 

ሆኖም ከላይ የተዘረዘሩ የወንጀል ጉዳዮች በተናጠል አስፈላጊነቱ ሲታመንበት ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡ 

Department Lead

ዘላለም ፈቃዱ ሠሙ

ዳይሬክተር ጀነራል