በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ተግባር እና ኃላፊነት

ቀደም ሲል ይህ ዳይሬክቶሬት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ የነበረ ሲሆን ስራው በባህርዩ ከወንጀል ጉዳዮች ክትትል ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው በመሆኑ፣ በዚህ ዘርፍ ስር የታዩ የወንጀል ጉዳዮች ከፍተኛ የመንግስት እና የህዝብ ሀብት የሚመዘበርባቸው እና በሀገር ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ከመሆናቸው አንጻር ስራውን በጥብቅ ቅንጅት በመፈጸም ውጤታማ ለማድረግ፣ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ካሉት ዳይሬክቶሬቶች ጋር ያለውን የጎንዮሽ ትስስር ታሳቢ በማድረግ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ የሀብት ማስመለስ ክትትል እና ድጋፍ የማድረግ ተግባር እና ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡

ይህ የስራ ክፍል የሀብት ጥናት ምርመራ ማስተባባሪያ፣ የሀብት ማስመለስ ማስተባባሪያ እና የንብረት አስተዳደር ክትትል ማስተባባሪያን ይዞ የሚከተሉት ተግባር እና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡- 

 1. ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ የወንጀል ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገራት በህግ መሰረት የሀብት ምርመራ ሥራ ያከናዉናል፣ የኃብት ግመታ እንዲካሄድ ያደርጋል፣ 
 2. በሙስና፣ በኢኮኖሚ እና በተደራጁ እና ድንበር ተሸጋሪ የወንጀል ተግባር የተገኙ የወንጀል ፍሬዎች፣ የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም ጥቅም ላይ የዋሉ ንብረቶች፣ ከወንጀል ከተገኘ ሀብት ጋራ የተቀላቀሉ ንብረቶች እንዲሁም በወንጀል የተገኙ ንብረቶችን በመጠቀም የተፈራ እንዲሁም ከገቢ በላይ የተገኘ ሀብት ያጠናል/ይመረምራል፣ በህግ አግባብ ያስመልሳ፣ ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በጋራ ይሰራል፣ 
 3. ጥቆማዎችንና ጠቋሚዎችን ይመዝግባል፣ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ለጠቋሚዎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ ለሚመለከተው ክፍል ያቀርባል፣ 
 4. በሕጉ አግባብ ለሽልማት /ወረታ/ ብቁ የሆኑ ጠቋሚዎች እና ምስክሮችን ለይቶ ተገቢው ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚያስችል ስርዓት እንዲቀረጽ ያደርጋል፣ ያስፈጽማል፣ 
 5. ሕግ በሚፈቅደዉ አግባብ ልዩ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም በወንጀል የተገኘ ሀብትንና የወንጀል ፈጻሚዎች ለመለየት የሚያስችሉ ማስረጃዎችን ያሰባስባል፣ 
 6. በሕግ አግባብ በህገ ወጥ መንገድ የተገኙ ወይም ተያያዥ ንብረቶችን ያሳግዳል፣ የታገዱ ንብረቶችን የሚያስተዳድር አካል እንዲሾም ያመለክታል፣ የንብረቶቹ አስተዳደር ይከታተላል፣ በንብረት አስተዳደሩ ለሚከሰት ጉድለት እርምጃ እንዲወሰድ ለፍርድ ቤት ያመለክታል፣ 
 7. በወንጀል ተግባር የተገኘ እና ከአገር ዉጭ የሸሸ ሀብት ለማስመለስ ከሕግ ጉዳዮች ዓለም ዓቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ጋር በመሆን መረጃና ማስረጃ ያሰባስባል፣ 
 8. ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ከሀብት ማስመለስ ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር የተሰጡ የፍርድ ቤት ትእዛዞችና ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ይከታተላል፣ መፈጸማቸውንም ያረጋግጣል 
 9. በወንጀል የተገኘ ሀብትን የወንጀል ፍርድን (Conviction Based) ወይም /እና የወንጀል ፍርድ ሳይኖር (Non-Convection Based) ሀብት ለማስመለስ ከወንጀል ክስ ጋር በተጓዳኝ ወይም በተናጠል በማቅረብ ያስመልሳል፣ 
 10. ከንብረቱን ማስመለስ ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው አካለት በሕግ መሰረት ድርድር ያደርጋል፤ የድርድር ዉጤቱ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ሲጸድቅ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ 
 11. በሕግ መሰረት የተወረሰ ንብረት ለሚመለከተው አካል ገቢ መደረጉን ያረጋግጣል፤ 
 12. የተቋሙንና የዘርፉን ዕቅድ መነሻ በማድረግ የስራ ክፍሉን ተግባራት ያቅዳል፣ አፈፃጸማቸውን ይከታተላል፣ ድጋፍ ይሰጣል፤ 
 13. ለስራ ክፍሉ የሚያስፈልገውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ግብአት እንዲሟላ ያደርጋል፣ ስራ ላይ መዋሉን ይከታተላል፣ 
 14. የስራ ክፍሉ ተግባራት የሚመሩበትን መመሪያዎች እንዲዘጋጁ ያደርጋል ፣ሲፀድቁም በአሰራሩ መሠረት መፈጸማቸውን ያረጋግጣል ፣ በየጊዜው እንዲሻሻሉ ሃሳብ ያቀርባል፤ 
 15. በስራ ክፍሉ ያሉ ባለሙያዎችን የክህሎት ክፍተት ለይቶ አቅማቸው የሚገነባበትን ስልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋል፤ የስራ ክፍሉን ሰራተኞችን የስራ አፈፃፀም ይመዝናል፤ 
 16. ከዘርፉ ኃላፊ ጋር በመመካከር ለስራ ክፍሉ ተልእኮ መሳካት አስተዋፅኦ ካላቸው ተቋማትና የሥራ ክፍሎች ጋር የሥራ ግንኙነቶችን ይፈጥራል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የመግባቢያ ስምምነት ይፈራረማል፣ በቅንጅት ይሰራል፤ 
 17. ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች ለመቅረጽ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባል፣ 
 18. ከስራ ክፍሉ ተልእኮ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ያደራጃል፣ 
 19. ለስራ ክፍሉ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን እና ቅሬታዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል ፣ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል፤ 
 20. የስራ ክፍሉን የስራ አፈፃፀም ይከታተላል፣ ይገመግማል፣ ከቡዱኖች ሪፖርት ይቀበላል ፣ ግብረ መልስ ይሰጣል፣ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዘጋጅቶ በወቅቱ ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፣ 
 21. በስራ ክፍሉ ተልእኮ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መድረክ ያዘጋጃል፣ያሳትፋል፣ 
 22. የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞች በተቀመጡ እሴቶች መሠረት በስነምግባር እና በባለቤትነት ስሜት እንዲሰሩ እና ውጤታማ እንዲሆኑ የኮቺንግ (Coaching) ሥራ ያከናውናል፣ በስራ ክፍሉ ያሉትን ሰራተኞች በስነምግባር እንዲገነቡ ያደርጋል፣ ጥሰት ሲፈፀም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያደርጋል፤ 

Department Lead

ጸጋ ዋቅጅራ ገንጅባ

ዳይሬክተር ጀነራል