ዜና

በህገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ወደ ውጭ አገር ለመላክ ከግለሰቦች ገንዘብ የተቀበለችው ተከሳች በጽኑ እስራት ተቀጣች

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ሕግ በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር ለመላክ ገንዘብ ከግለሰቦች ተቀብለሻል ባላት ግለሰብ ላይ ክስ መስርቶባት ክርክሩ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ተከሳሽ ደመቀች ማጉጄ አቤቱ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 27/1/ እና በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 11/1/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በዐቃቤ ሕግ ስድስት ክስ ቀርቦባታል፡፡ 

ተከሳሽ ወደ ውጭ አገር ሰውን ለስራ ለመላክ ፍቃድ ሳይኖራት ቀኑ በውል ተለይቶ ባልታወቀ ከሀምሌ ወር 2013 እስከ መስከረም ወር 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ 6 ተበዳዮችን ወደ ጆርዳን አገር ልኬ ስራ አስቀጥራችኋለሁ ለዝግጅቱ እና ለህክምና ምርመራ ብር ትከፍላላችሁ በማለት ፓስፖርት እና ፎቶግራፍ በመቀበል፣ ከ1ኛ ተበዳይ 29 ሺ 500 ብር፣ ከ2ኛ ተበዳይ 32 ሺ 500 ብር፣ ከ3ኛ ተበዳይ 33 ሺ 500 ብር፣ ከ4ኛ ተበዳይ 39 ሺ ብር፣ ከ5ኛ ተበዳይ 25 ሺ ብር፣ ከ6ኛ ተበዳይ 23 ሺ ብር ተቀብላለች፡፡

ቀጥሎም ታህሳስ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ጆርዳን አገር ስለምትሄዱ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቀድማችሁ መድረስ አለባችሁ ብላ በመንገር እና ከሌሎች የግል ተበዳዮች ጋር ታክሲ በማሳፈር ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ሲሆን ቦሌ አየር ማረፊያ ካደረሰቻቸው በኋላ ግብረ-አበሯ የሆነውና ለጊዜው በቁጥጥር ስር ያልዋለ ግለሰብ የበረራ ትኬት ይዞ እየመጣ ነው በሚል ሲጠብቁ ሳይመጣ ቀርቶ የበረራ ሰዓት አልፎ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ሲሆን ነገ ትሄዳላችሁ አሁን አልጋ ይዘን ታድራላችሁ በማለት እየተመለሱ እያለ በጸጥታ አካላት የተያዙ በመሆኑ ተከሳሽ በፈፀመችው በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ሙከራ ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ 

ተከሳሽ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ቀርባ የተከሰሰችበት ክስ በችሎት ተነቦላት ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለቷ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንድትከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮችን አቅርባ ያሰማች ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበባትን ክስ መከላከል ባለመቻሏ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሿ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠትና የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ30 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ እንዲሁም ከህዝባዊ መብቶቿ ለ5 ዓመት ታግዳ እንድትቆይ ሲል ወስኗል፡፡