ዜና

ፍትሕ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት እቅድ 6 ወራት አፈፃፀሙን ገመገመ

ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት እቅድ 6 ወራት  አፈፃፀሙን የተቋሙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ሰራተኞች በተገኙበት የካቲት 08 ቀን 2016 ዓ.ም ገምግሟል፡፡ 

የተቋሙን የ6 ወር አፈፃፀም ሪፖርት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ መንግስቴ ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱም የክርክር መዝገቦች (በፍትህ ሚኒስቴር 24,883 እና በክልሎች ፍትህ ቢሮ 65,163) በአጠቃላይ 92,011  የክስ መዝገቦች  ክርክር ተደረጎባቸው  43,206 መዝገቦች ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን  41,376 መዝገቦች የቅጣት ውሳኔ ያገኙ መሆኑን እንዲሁም 1,830 መዝገቦች  ደግሞ በነጻ እንዲሰናበቱ ውሳኔ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

የመንግስትና የህዝብን ፍትሐብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር በገንዘብ ሲተመን ከ23 ቢሊየን ብር በላይ እና 14 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ክርክር መደረጉን፣ በግማሽ ዓመቱ 58 ሺህ 4 መቶ 78 በማረሚያ ቤት እና በፖሊስ ማረፊያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ታራሚዎች መጎብኘታቸውን እንዲሁም ለ6 ሺህ 13 ዜጎች ነፃ የሕግ አገልግሎት የተሰጠ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ምርመራቸው ተጠናቆ የሚቀርቡ መዝገቦችን (በፍትህ ሚኒስቴር 27,168 እና  በክልሎች ፍትህ ቢሮ 69,007) በአጠቃላይ  እንደ ሃገር 98,348  የምርመራ መዝገቦች በዐቃቢያነ ህግ እጅ የነበሩ ሲሆን 93,991 መዝገቦች ላይ ዐቃቤ ህግ የተለያዩ ውሳኔዎችን የሰጠ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ከሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አንጻር የሽግግር ፍትህ ሀገራዊ ፖሊሲ ይዘት ግብዓት ሊሆኑ በሚችሉበት አግባብ በመሰነድ እና በፖሊሲ አማራጮቹ ላይ የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶችን ፣ ማጠቃለያዎችን እና ምክረ ሃሳቦችን የያዘ ዝርዝር ሪፖርት ለህዝብ ይፋ መደረጉም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

ቀጥሎም የኢትዮጵያ የፍትህ አካላት የ3 ዓመት ትራንስፎርሜሽን እቅድ የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ አማካሪ አቶ አማኑኤል ታደሰ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ በመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችና ለተሰጡ አስተያቶች በፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና  በፍትሕ ሚኒስቴር የሶስቱም ዘርፎች ሚኒስትር ዴኤታዎች መድረኩ እየተመራ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን  ለቀጣይ 6 ወራትም የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡

በመጨረሻም የቀድሞ የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ለነበሩት አቶ አለምአንተ አግደው እና አቶ ፍቃዱ ፀጋ የምስጋና እና የሽኝት መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡