ዜና

“ተቋሙን ዲጅታላይዝድ በማድረግ በኩል ባለፉት ወራት የበለፀጉት ከ10 በላይ መተግበሪያዎች ትርጉማቸዉ የጎላ ነዉ” ክቡር ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ

ሚኒስትር ዴኤታዉ ይህንን የተናገሩት ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማዘመን እና አሰራሩን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ከያዛቸው ፕሮጀክቶች መካከል ወደ ተቋሙ የሚመጡ ትላልቅ ሃገራዊ የሆኑ ፍትሐብሔራዊ ጉዳዮችን፣ የህግ ረቂቅ ስርዓት መከታተያ ዳሽ ቦርድን እና ዘመናዊ የዐቃቢያነ ሕግ መረጃ ሥርዓትን፣ የህግ እና ተዛማጅ ሥልጠናዎች ማስተዳደሪያ ሲስተም እና ተቋሙ ለሕብረተሰቡ የተለያዩ  መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርግበት ዌብሳይት አስገንብቶ  አርብ የካቲት 01 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ባስመረቀበት ወቅት  ነዉ፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴርን ዲጅታላይዝድ ለማድረግ ባለፉት ጊዚያቶች በርካታ ሲሰተሞች በልፅገዉ ተግባር ላይ የዋሉ ሲሆን እነዚህ ተግባራትም የዲጅታላይዜሽንና የአዉቶሜሽን ስራዎችን ትርጉም ባለዉ መልኩ ከፍ የሚያደርጉ ናቸዉ ሲሉ ያከሉት ሚኒስትር ዲኤታዉ በዚህም የ116 ዓመት ታሪክ ባለቤት የሆነዉን የፍትህ ሚኒስቴርን አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ፣ ጊዜ ቆጣቢ ፣ቀልጣፋ እና ተደራሽ  እንዲሆን እንደሚያስችለዉም ተናግረዋል፡፡ 

ተቋሙ በዛሬዉ እለት ይፋ ያደረጋቸዉን የhuman resource management system(HRMS)፣  dashboard training managements system (TMS)፣ website  መተግበሪያዎችን ጨምሮ ካሁን በፊት የታራሚዎች የይቅርታ መጠየቂያ፣ የጥብቅና ፈቃድ እና እድሳት፣ የቅሬታና አቤቱታ አያያዝ፣ የዓቃቢያነ ህግ መመዘኛ እና ሌሎች በጥቅሉ ከ10 በላይ መተግበሪያዎችን በማልማት ወደ ስራ ማስገባቱን ክቡር ዶክተር ኤርሚያስ ተናግረዋል፡፡

በዛሬዉ እለት ይፋ ከተደረጉት አራት ሲስተሞች መካከልም የዳሽቦርድ የህግ ማርቀቅ፣ሀግ ምክር የፍትሃብሄር ጉዳዮች የሚያነሱ ተቋማት ወደ ፍትህ ሚኒስቴር መምጣት ሳይጠበቅባቸዉ ባሉበት ሆነዉ ጥያቄዎቻቸዉን የሚቀርቡበትና ምላሽ የሚያገኙበት ሲስተም ሲሆን በዚህም ከ500 በላይ ተቋማት ይገለገሉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

በተያያዘም የሰዉ ሀብት አስተዳደር ሲስተም እስከ ግለሰብ ያለዉን አጠቃላይ የእለት ተእለት ስራ የሚያሳይና አጠቃላይ ተቋማዊ መዋቅርን የያዘ በመሆኑ ግለሰብ  የሚሰራዉን ስራ ጭምር ለመመዘን የሚያስችል ግልፅ ወጭ ቆጣቢና ቀልጣፋ አሰራርን የሚፈጥር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የስልጠና አሰጣጥን የሚመለከተዉ የTMS ሲስተምም ለተቋሙ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ ያለዉና  በአዲስ መልክ የበለፀገዉ website የፍትሕ ሚኒስቴር አጠቃላይ እንቅስቃሴና ምንነት በግልፅ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆንበት ትላልቅ ስራ መሆናቸዉ ተመላክቷል፡፡

እነዚህ ሁሉ ተግባራት በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘዉን የሶስት አመት የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ፍኖተ ካርታ ከያዛቸዉ 10 አምዶች ዉስጥ አንደኛዉ በሆነዉ ዉጤታማና ያደገ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ አጠቃቀምን በፍትህ ዘርፍ እዉን ማድረግ የሚለዉን አምድ እዉን ለማድረግ እንደ ጉልህ እርምጃ ተደርጎ እንደሚወሰድ የጠቆሙት ሚኒስቴር ዲኤታዉ በቀጣይም እስካሁን ከተሰሩ ስራዎች በተጨማሪ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ተግባራዊ የሚደረገዉን Crimsን የማልማት ስራን በበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል ተግባራዊ እንደሚደረግ በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

እስካሁን የበለፀጉት ሲስተሞቸና መተግበሪያዎች እዉን እንዲሆኑና ለዉጥ እንዲያመጡ ለማስቻልም ህብረተሰቡ የበለጠ እንዲያዉቃቸዉ የማስተዋወቅ ስራን መስራት እንደሚገባ የገለጹት ክቡር ዶክተር ኤርሚያስ በአግባቡ በመጠቀምና ተግባር ላይ በማዋል ለዉጤታማነታቸዉ በትኩረት መሰራት እንደሚያስፈልግ እና ህብረተሰቡም እነዚህን መተግበሪያዎች በመጠቀም ጊዜዉንና ጉልበቱን በመቆጠብ ከእንግልት ራሱን እንዲታደግ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በእነዚህ ስራዎች ለተሳተፉ የሀገር በቀል የሶፍት ዌር አበልፃጊዎች ለሰሩት ስራና በፍትሕ ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ላደረጉት ጉልህ አስተዋፅኦና በጥቅሉ በስራዉ ለተሳተፉ አካላት  በፍትሕ ሚኒስቴር ስም ላቅ ያለ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡