በምክክር መድረኩ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የፍትህ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀምና የሱፐርቪዥን ሪፖርት አቅርበዋል። በቀረበው ሪፖርት ላይ የተለያዩ አስተያየቶችና ሃሣቦች ተሰጥተው በተሣታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በውይይቱ በሰጡት አስተያየት፤ ህብረተሰቡ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ሮሮ እያሰማ ስለሆነ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የሚነሳውን የጥራት ችግር ለመቅረፍ ሕጋዊ አሠራርን የሚከተሉ የፍትህ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። የተከበሩ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አክለውም ህብረተሰቡ የፍትህ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት እምነት ኖሮት ወደ ፍትህ ተቋማት እንዲመጣ ለማድረግ የፍትህ ተቋማቱ በቴክኖሎጂ ተደግፈው ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አመላክተዋል።
የተከበሩ አፈጉባዔው አክለውም የፍትህ ሥርዓቱን ማዘመን ለአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ወሳኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የሚነሳውን ሮሮ ለማስቀረት ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ የፍትህ አካላት በቅንጅት ሠርተው ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ክቡር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ ህብረተሰቡ በፍትህ ሥርዓቱ እምነት እንዲኖረው በየደረጃው ባሉ የፍትህ አካላት የትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ እና የክልል አፈ ጉባኤዎችም ይህን ጥረት በመደገፍ የጀመሩትን ክትትልና ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።