ዜና

እጩ ዓቃቢያነ ህግ ወደ ስራ ስትሰማሩ ከእያንዳንዱ መዝገብ ጀርባ የተበደለ እና ፍትህ የተጠማ ሰዉ እንዳለ በማሰብ በኃላፊነት ስሜት ሙያችሁን አክብራችሁ ልትሰሩ ይገባል

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዬን ጢሞቲዎስ 

ፍትሕ ሚኒስቴር ወደ ተቋሙ ለሚቀላቀሉ አዳዲስ እጩ ዓቃቢያነ ህግ ስልጠና በመስጠት ላይ ነዉ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ወደ ተቋሙ ለሚቀላቀሉ 104 ለሚሆኑ አዳዲስ እጩ ዓቃቢያነ ህግ የተቋሙን አጠቃላይ ገፅታ የሚያመላክትና ለአምስት ቀናት የሚዘልቅ የመተዋወቂያ ስልጠና በዛሬዉ እለት መስጠት ጀምሯል፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እጩ ዓቃቢያነ ህግ እንኳን ወደተቋማችን መጣችሁ ካሉ በኋላ ተቋሙ ባለፉት አመታት ከተለያዩ የህግ ትምህርት ቤቶች ባስመዘገቡት ዉጤት የተመረጡ ጀማሪ የህግ ባለሙያዎችን በማምጣትና አወዳድሮ በመቅጠር ሂደት ዉስጥ መሆኑን ጠቁመዉ ይህ የሆነበት ዋነኛዉ ምክንያትም በፍትህ ሚኒስቴር የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከፍ እንዲያደርጋቸዉ ታስቦና ሀገርንና ህዝብን በብቃትና በተሻለ መልኩ ብሎም በስነ ምግባር በማገልገል በኩል የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት በማመን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ሚኒስትሩ አክለውም ከዚህ ባለፈ በተቋሙ የሚሰሩ ማናቸዉንም የህግ ስራዎች ሲሰሩ አቅማችሁን በመጠቀም ጥራት ባለዉ መልኩ ትሰራላችሁ ብለን እናምናለን ሲሉ እጩ ዓቃቢያነ ህግ በበኩላችሁ ወደ ተቋሙ በመቀላቀላችሁ ከደመወዝ ባለፈ በሂደት በምታካብቱት ልምድ የተሻለ ግንዛቤ የምታገኙበትና በዚህም ከትምህርት ቤት ያገኛችሁትን እዉቀት በተግባር በመፈተሸ ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ ክህሎታችሁን ለማዳበርና በተለይም በልምድ ራሳቸዉን ካሳደጉ የተቋሙ ነባር ባለሙያዎች ለመማር ትልቅ እድል በመሆኑ ልትጠቀሙበት ይገባል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም እጩ ዓቃቢያነ ህግ ወደ ስራ ስትገቡ ለስነ ምግባር በመገዛትና ለሙያችሁ ታማኝ ልትሆኑ ይገባል ካሉ በኋላ በተለይም ከምትሰሯቸዉ እያንዳንዳቸዉ መዛግብት ጀርባ የተበደለና ፍትህ የሚናፍቅ ሰዉ እንዳለ በማሰብ በኃላፊነት ስሜት ሙያችሁን አስከብራችሁ በሀቀኝነትና በእዉነት ትክክለኛዉን ሰራ ልትሰሩ ይገባል ሲሉ በአጽንኦት አሳስበዉና መልካም የሙከራና የስልጠና ጊዜ ተመኝተዉ ንግግራቸዉን ቋጭተዋል፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን በበኩላቸዉ እጩ ዓቃቢያነ ህግ በህይወታችሁ አዲስ ምእራፍን ለምትጀምሩበት ቀን እንኳን አደረሳችሁ ካሉ በኋላ ወደ ተቋሙ ስትቀላቀሉ ህግን በማስከበር በኩል ትልቅ የህዝብ ኃላፊነት እንዳለባችሁ በማመን ራሳችሁን እንድታዘጋጁ ሲሉ ለዚህም የግል ትጋት ወሳኝ በመሆኑ መረጃዎችን በማወቅ፣የሚጠቅመዉን በመለየትና፣በማንበብ አዉቃችሁና ተገንዝባችሁ ለስራችሁ መጠቀም ይኖርባችኋል ካሉ በኋላ የአሁኑ ስልጠና አጠቃላይ የተቋሙን ሁኔታ ለማመላከት የታሰበ መሆኑንና በቀጣይ ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ረዘም ያለ ስልጠና እንደሚዘጋጅ ገልፀዋል፡፡

የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው ከብዙ ሰዎች ጋር ተወዳድራችሁና ዓቃቤ ህግነትን መርጣችሁ ሰለ መጣችሁ እናመሰግናለን ካሉ በኋላ የዓቃቢያነ ህግ ስራ ዘርፈ ብዙ መሆኑንና በተለይም ያለአግባብ የተከሰሰን ሰዉ ተከራክራችሁ ነፃ የምታወጡበትና ያጠፋን ሰዉ ከሳችሁ የምታስቀጡበት ከመሆኑ በተጨማሪ የህዝብን ንቃተ ህግ በማዳበር፣የጥናትና ምርምር ስራዎች በመስራትና በሌሎች ተግባራት ነፃ ሆናችሁ ፍትህን ልታረጋግጡበት የምትችሉበት ሞያ መሆኑንና ለዚህም ስራ በተለይም ባለጉዳይን በማክበር በርትታችሁ በመስራት የህዝቡን የፍትህ ጥማት እንደምታረጋግጡ እምነቴ ነዉ ሲሉ በንግግራቸዉ ገልፀዋል፡፡

በስልጠናዉም የፍትሕ ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባር፣  አሰራርና አደረጃጀት፣ የዓቃቢያነ ህግ ሙያዊ ስነ ምግባርና መተዳደሪያ ደንብ፣ የወንጀል ምርመራ ክስ ዝግጅትና ፍትሐብሄር የሚሉና ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡