ዜና

ከ14 ሺ ግራም በላይ የኮኬይን እፅ ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ ዜጋ በፅኑ እስራት ተቀጣ

አሉይሲኡስ ኦኔን የተባለ የናይጄሪያ ዜግነት ያለው ተከሳሽ ልዩ ፈቃድ ሳይኖረው በህግ የተከለከሉ እፆችን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር አስቦ ከብራዚል አገር ሳኦፖሎ ከተማ በመነሳት የኢትዮጵያን አየር መንገድ በመጠቀም ወደ ናይጄሪያ አገር ሌጎስ ከተማ ለመሄድ ህዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት ሲሆን ቦሌ አለም ዓቀፍ ኤርፖርት ለትራንዚት ባረፈበት ወቅት በተደረገበት ፍተሻ ሻንጣው ውስጥ ደብቆ 5 እሽግ ወይም 14‚319.69 ግራም የሚመዝን ኮኬይን አደገኛ እፅ ተገኝቶበታል፡፡ 

በመሆኑም ሰዎችን ሱስ በማስያዝ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መንስኤ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደውን ኮኬይን እፅ ፈቃድ ሳይኖረው ይዞ እየተጓዘ የተገኘ በመሆኑ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ወንጀል ሕግ አንቀጽ 525/1/ለ/ ስር የተደነገገውን በመተላለፍ አደገኛ እፆችን ማዘዋወር ወንጀል ክስ መስርቶበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ተከሳሹ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት በወቅቱ ይዞት በነበረው ሻንጣ ውስጥ ምንም አይነት ኮኬይን ይዞ እንዳልነበር የገለፀ ሲሆን ዐቃቤ ህግም በጉዳዩ ላይ የሚያስረዱ የህግ ምስክሮችን አቅርቦ በማሰማት፣ ተከሳሹም በቀረበበት ክስ መሰረት እንዲከላከል ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ቢሰጠውም የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት ባለማቅረቡ የመከላከል መብቱ ታልፎ በቀረበበት ክስ ስር በማስረጃ እንደ ክሱ አቀራረብ የተረጋገጠበት በመሆኑ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ20 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኗበታል፡፡