ዜና

አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቶችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ምክክር ተደረገ

የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሰረት ወደ ፍትህ ሚኒስቴር የተቀላቀሉት የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ ችሎት፣ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና የምርት ገበያ አስተዳደራዊ ችሎት ስራ ከጀመሩ 2 ዓመት ቢያስቆጥሩም በሚፈለገው ደረጃ ቀልጣፋና ውጤታማ ስራዎችን እያከናወኑ ባለመሆኑ በችግሮቹና በቀጣይ የስራ ተልዕኮዎች ላይ ያለመ ምክክር ተደርጓል፡፡
ምክክሩን የመሩት የመንግስት የህግ እና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ አስተዳደራዊ ችሎቶቹ ስራቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዳያከናውኑ እንቅፋት የሆኑ የአደረጃጀት፣ የአሰራርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳቦችን በመቀበል ስራውን የተሻለ አደረጃጀትና የስራ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ መፍትሄዎችን አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር ያለውን የስራ መስተጋብር በማጠናከርና ቀጣይነት ያለው ምክክር በማድረግ፣ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ያለውን የተሻለ ልምድ እና ተሞክሮ አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመጠቀምና አስተዳደራዊ ችግሮችን በአፋጣኝ በመፍታት ችሎቶቹ የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አጽዕኖት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡
ችሎቶቹ በዋናነት በሸማቹ ማህበረሰብ፣ በነጋዴው ማህበረሰብ እና በተቆጣጣሪ የመንግስት ተቋማት የሚቀርቡ ከንግድ ውድድር፣ ሸማቾች ጥበቃ እና ከምርት ገበያ የግብይት ስርዓት ጋር በተገናኘ የሚቀርቡ ክሶችን በመቀበል ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ከክቡር የመንግስት ህግ እና ፍትህ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታው በተጨማሪ የፌዴራል ግብር ይግባኝ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው እና የፍትህ ሚኒስቴር አመራሮች በመገኘት ማብራሪያና ምክረ ሀሳቦችን አጋርተዋል፡፡
በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የሶስቱ ችሎቶች ለአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና ሲባል የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ ወደሚገኝበት ጨለቀቅ ህንጻ የተዘዋወረ መሆኑን በመግለጽ የችሎቶቹን አገልግሎት ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሜክሲኮ ጨለለለቅ ህንጻ ላይ በሚገኘው ቢሯቸው መስተናገድ የሚችል መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ጉዳዮች ዙሪያ ከማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከማረሚያ ቤት ኮሚሽኑ ጋር ስራዎችን በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙንና በሰነዱ ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ ለማረሚያ ቤት ኮሚሽን ባለሙዎች እና ታራሚዎች ከንቃተ ህግ ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን መስጠት መሆኑን በስልጠናው የመክፈቻ ንግግራቸው የገለጹት በፍትህ ሚኒስቴር የንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ወርቁ ናቸው።

ስልጠናው የሚዳስሰው ታራሚን ማረም፣ ከህብረተሰቡ መልሶ መቀላቀል እና የሰብአዊ መብት መከበር የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችን እንደሆነ ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡ አያይዘውም የማረሚያ ቤት ስራ እጅጉን ከሰብአዊ መብት ጋር የተቆራኘ መሆኑን በማውሳት በማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች የወንጀል ህጉን አላማ ለማሳካት ብሎም ግቡን እንዲመታ እና ታራሚዎች በሚፈለገው ልክ ታርመውና ታንጸው እንዲወጡ ለማስቻል ስራዎችን በጋራና በተቀናጀ መልኩ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የስልጠናውም ዓላማ አዲስ ዕወቀት ማግኘት፣ ሰልጣኞች የእርስበርስ ልምድ መለዋወጥ እንዲችሉ ማድረግ እና ቀደም ሲል ስልጠናውን ለወሰዱት ደግሞ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የበለጠ ግንዛቤ ማግኘት የሚያስችል እንደሆነ አቶ እንዳልዛቸው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የስልጠናው ተሳታፊዎች የስነ-ምግባርና ባህሪ ቀረጻ ባለሙያዎች፣ የታራሚዎች ፍትህ አስተዳደር እና የታራሚዎች የፍትህ ጉዳይ አስፈጻሚ ባለሙያዎች ሲሆኑ ስልጠናው ለእነዚህ አካላት የስራ ሁኔታ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የህግ ታራሚዎች ህጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው እና በህግ ሊጠበቁላቸው እንደሚገባና ታራሚዎችን በአግባቡ አርሞ፣ አንጾ፣ ሰላማዊ፣ ህግን እና የህብረተሰቡን ዕሴቶች የሚያከብሩ እንዲሆኑ ለማስቻል የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን የገለጹት በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የተአድሶና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዝመራው አብደታ ናቸው፡፡ አክለውም ስልጠናው የክህሎት ክፍተቶችንም የሚሞላ እንደሆነ አውስተዋል።

ስልጠናው በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዐቃቤያነ ሕግ አቶ መዝሙር ያሬድ እና አቶ ተሰማ ግደይ የሚሰጥ እንደሆነና በስልጠናው የተካተቱ ርዕሰ ጉዳዮችም ከሰልጣኞች የዕለት ተዕለት ስራቸው ጋር የተቀራኙ በመሆናቸው ሰልጣኞች ስልጠናውን በትኩረት መከታተል እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡