ዜና

የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች የህዝብ ምክክር ሂደት አፈፃፀም እና በህዝብ አስተያየት የተመላከቱ ዋና ዋና ግኝቶች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

የሽግግር ፍትህ የባለሙያዎች ቡድን የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች የህዝብ ምክክር እና ግብዓት ማሰባሰብ ሂደት አፈጻጸም ፣ በተገኙ የሕዝብ አስተያየቶች እና ግብዓቶች የተመላከቱ ዋና ዋና ግኝቶች እንዲሁም በቡድኑ ምክረ ሃሳብ ዙሪያ ታህሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በሀገራችን የተለያዩ ሀይሎች እርስ በእርስ እና ከመንግስት ጋር ባደረጉት እና በሚያደርጉት ግጭት መነሻነት እንዲሁም ከግጭት አውድ ውጪ በነበሩ ኩነቶች በርካታ ዜጎች ሰፊ እና ተከታታይነት ላለው ከባድ የመብት ጥሰት፣ መፈናቀል እና እንግልት መዳረጋቸውን የሚያመላክቱ በርካታ ሪፖርቶች የወጡ በመሆኑ የሀገረ መንግስቱን ግንባታ ከማሳለጥ፣ ዘላቂነቱን ከማረጋገጥ እና በሰብዓዊ መብቶች እና የህግ የበላይነት መሰረታዊ መርሆዎች ላይ የተዋቀረ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ ግንባታና ሽግግር እውን ከማድረግ አንፃር የሽግግር ፍትህ ስርዓትን መቅረፅ እና ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የሽግግር ፍትህ የባለሙያዎች ቡድን ገልጿል፡፡

ከሀገራዊ ፍላጎት በመነሳት የቅድመ ረቂቅ ፖሊሲ ህዝባዊ ምክክሮችና ግብዓት ማሰባሰብ ስራዎችን የረቂቅ ፖሊሲ እና የድህረ ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት ተግባራትን ለማከናወን ሙሉ ኃላፊነት የተሰጠውና የተለያዩ ምሁራንና ባለሙያዎችን ያካተተ 13 አባላት ያሉት ነፃ እና ገለልተኛ የሆነ የሙያተኞች ስብስብ “የሽግግር ፍትህ ባለሙያዎች ቡድን” ህዳር 2015 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲደራጅ መደረጉ በመግለጫዉ ተጠቁሟል፡፡ 

የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች የህዝብ ምክክር እና ግብዓት ማሰባሰብ ሂደት ዓላማዎች በሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ላይ በክልላዊ እና ሀገር አቀፍ መድረኮች እንዲሁም በፅሁፍ የተሰበሰቡ ግብዓቶችን በማደራጀት እና በመተንተን ለሚዘጋጀው የሽግግር ፍትህ ሀገራዊ ፖሊሲ ይዘት ግብዓት ሊሆኑ በሚችሉበት አግባብ መሰነድ እና በፖሊሲ አማራጮቹ ላይ የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶችን ፣ ማጠቃለያዎችን እና ምክረ ሃሳቦችን ዝርዝር ለህዝብ ይፋ በማድረግ የሂደቱ ባለቤት የሆኑትን የኢትዮጵያ ህዝብ ፣ መንግስት፣ ባለድርሻ አካላትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት ሙሉ መረጃ እንዲኖራቸው ማስቻልና በዚህም የሂደቱን ግልፅነት ፣ ተዐማኒነት እና ተቀባይነት ማረጋገጥ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የባለሙያዎች ቡድኑ የምክክር እና የግብዓት ማሰባሰብ ስራዉን በይፋ ከጀመረበት ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ሁሉንም ክልሎች እና ሁለቱን የከተማ መስተዳድሮች ያሳተፈ ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ያካሄደ ሲሆን እንዲሁም በልዩ ሁኔታ በተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ብቻ ያተኮሩ ተጨማሪ መድረኮች መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡ በሁለቱም ሂደቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ግብዓት ለማሰባሰብ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡

በተካሄዱት ሀገር አቀፍ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓትን የምትከተል ሃገር እንደመሆኗ መጠን በሽግግር ፍትህ ትግበራ ሂደት ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የሚኖራቸውን ሚና በግልፅ መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ረገድ በተካሄዱት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ ሁሉም ተሳታፊዎች ሊባል በሚችል መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሊቀረፅ እንደሚገባ ፣ በፖሊሲ ትግበራ ሂደቱ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች አስፈላጊ ትብብር እና ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው እንዲሁም የራሳቸውን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሊቀርፁም ሆነ ሊተገብሩ እንደማይገባ በስፋት መንፀባረቁን ለዚህም በዋናነት የተሰጡት ምክኒያቶች የሽግግር ፍትህ ስራ በአጠቃላይ ዜጋ ተኮር እና ሀገራዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ፣ ብዙ ክልሎችን በአንድ ጊዜ ያቅፋል እንዲሁም በሽግግር ፍትህ ሂደቱ ተግባራዊ የሚደረጉ ብዙዎቹ ህጎች በፌደራል መንግስት ስልጣን ማእቀፍ ስር የሚወድቁና ሀገራዊ የተፈፃሚነት ወሰን ያላቸው ናቸው የሚሉ መሆናቸውን መግለጫው ያሳያል፡፡ 

ሆኖም ግን ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች የሀገራዊ ችግሮቹ አካል እንደመሆናቸው መጠን ዝርዝሮቹ በጥንቃቄ እየተለዩ የመፍትሄዉ አካል መሆን እንደሚኖርባቸው ለዚህም የሚያመች አሳታፊ ስርዓት ሊቀረፅ እንደሚገባ ተሳታፊዎች በአፅንኦት ማንሳታቸው ተመላክቷል፡፡

በመግለጫው ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች በሽግግር ፍትህ የባለሙያዎች ቡድኑ ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡