በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጉዳዮች መከታተያ ዳይሬክቶሬት የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወር የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ አካሂዷል፡፡ በሪፖርቱም ላይ የየቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች ተገኝተው ውይይት አድርገውበታል፡፡
በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጉዳዮች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌቱ ታደሰ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወር አፈፃፀም ሪፖርቱን ሲያቀርቡ እንዳሉት በፖሊስ ምርመራቸው ተጠናቆ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለውሳኔ ቀርበው መወሰን ካለባቸው 23,569 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 22,811 መዝገቦች ላይ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በዐቃብያነ ሕግ ውሳኔ ተስጥቶባቸዋል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በሁሉም የወንጀሎች ክርክር መዛግብት የመርታት ምጣኔን አስመልክቶ በክርክር ላይ ከነበሩት 21,978 መዛግብት እና 31,944 ተከሳሾች ውስጥ ፍርድ ቤት በ6,137 መዛግብት እና በ7,240 ተከሳሾች ላይ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፣ በ5,970 መዛግብት እና በ7,021 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት፣ በ167 መዛግብት እና በ219 ተከሳሾች ላይ ነፃ በማለት ፍርድ መሰጠት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በፍትሀብሔር ጉዳዮች የሚሰጥ ፍርድ ማስፈፀምን በተመለከተ ሲያብራሩ 12,141,055.27 ብር በዓይነት እና በገንዘብ የሚተመን በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎባቸው ለፍርድ ባለመብቶች እንዲወሰን በማድረግ ከዚህም ውስጥ 4,400,006.28 ብር ለፍርድ ባለመብቶች እንዲከፈል መደረጉን አዉስተዋል።
አቶ ጌቱ ታደሰ ከሰብዓዊ መብት ማስከበር ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ 6 ወር ውስጥ 11,869 በማረፊያ ቤት የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን እና ድሬዳዋ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎችን ጉብኝት በማድረግ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ መስጠት ተችሏል ያሉ ሲሆን፣ 7,114 ተገልጋዮች አገልግሎት እንዲሰጣቸው ጠይቀው 5,792 የሚሆኑ አገልግሎቱን በዜጎች ቻርተር በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ምላሽ ያገኙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች 604 አቤቱታዎች ቀርበው ለ578ቱ ምላሽ የተሰጠባቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርትም የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን በተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ተገቢውን ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፋት መልዕክት ዐቃቤያነ ሕግ ሙያው የሚጠይቀውን ስነ-ምግባር አክብረው ስራቸውን ማከናወን እንዳለባቸው በማስገንዘብ ከመዝገብ ጥራት፣ ምርመራ፣ ክስ መመስረት እና ፍርድ ቤት ቀርቦ እስከ መከራከር ድረስ በተገቢው መሰራት እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡