ዜና

ምግብ አብላኝ አላበላህም በሚል በተፈጠረ አለመግባባት ሟችን በኮብልስቶን ድንጋይ በመምታት የገደለው ተከሳሽ በፅኑ እስራት ተቀጣ

ብርሃኑ ገበየሁ የተባለው ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ ሀምሌ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 8፡00 ሰዓት ሲሆን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 አየር ጤና ሸዋ ሱፐር ማርኬት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ምግብ አብላኝ አላበላህም በሚል በተፈጠረ አለመግባባት ሟች ማሙሽ ቤቴሌ የተባለውን በኮብልስቶን ድንጋይ ደረቱ ላይ በመምታቱ ምክንያት ሟች የወደቀና ወዲያውኑ ህይወቱ በማለፉ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ተራ የሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት ማቅረብ ባለመቻሉ በተከሰሰበት የህግ ድንጋጌ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠትና የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡