ዜና

የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ ሲፀድቅ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ (Road Map) ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

በ1949 ዓ.ም ወጥቶ የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ዘመኑ ከደረሰበት አዳዲስ አስተሳሰቦች፣ የቴክኖልጂ ዕድገቶችና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ፅንሰ ሃሳቦች ጋር የሚጣጣም ሆኖ ባለመገኘቱ በ1997ቱ የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ የተሻረ ቢሆንም በአንፃሩ ይህንን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ለማስፈፀም በ1954 ዓ.ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ሳይሻሻል እስከ አሁን ድረስ በስራ ላይ ይገኛል፡፡ 

በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ የፍኖተ ካርታውን መጀመር አስመልቶ ባስተላለፉት መልዕክት በ1954 ዓ.ም የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ለማሻሻል በተደረገ ጥረት “የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርዓትና ማስረጃ ሕግ” ረቂቅ በፍትሕ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ይሁንታ በማግኘቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ እንደሚፀደቅ እየተጠበቀ መሆኑን አስታውሰው ሕጉ ሲፀድቅ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ በርካታ የአሰራር፣ የአደረጃጀት፣ የወንጀል ጉዳዮችን የመመርመር፣ የመክሰስ እና አከራክሮ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን እና መሰል ጉዳዮች ላይ ለውጦችን የሚያመጣ በመሆኑ አተገባበሩን በፍኖተ ካርታ መምራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ 

ሚኒስትር ዴኤታው በገለጻቸው ፍኖተ ካርታው ሕጉ ሲፀድቅ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ እና በተለያዩ የፍትህ ተቋማት መዘጋጀት እና መፅደቅ ያለባቸው መመሪያዎች፣ ማኑዋሎች እና ዝርዝር የአሰራር ሥርዓቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር የሚያመለክት ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደ አዲስ መቋቋም የሚገባቸው አደረጃጀቶችን የሚመላክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአማራጭ ቅጣቶች ማስፈጸሚያ ሥርዓቶች፣ የታረሚያዎችን መልሶ መቀላቀል ስራ ተቋም እና መሰል አደረጃጀቶች የትኞቹ እንደሆኑ እና ስለሚደራጁበት አግባብ በዝርዝር ከሚመላከቱ ጉዳዮች መካከል በአብነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፍኖተ ካርታው በሕጉ አተገባበር ሂደት የክልሎች እና የፌዴራል የፍትህ ተቋማት ሚና፣ በፌዴራል እና በክለሎች የሚገኙ ፍትህ አካላት ባለሙያዎች የስልጠና ሁኔታ እና የስልጠና አይነቶች እንዲሁም እነዚህ ተግባራት የሚከናወኑበትን ጊዜ እና የሚያስፈፅሙ አካላትን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንዲይዝ ተደርጎ የሚዘጋጅ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በሕጉ አተገባበር ሒደት የባለ ድርሻ አካላት፣ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናን በዝርዝር የሚያስቀምጥ ስለመሆኑ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በገጻቸው አንስተዋል፡፡ 

የወንጀል ሕግ-ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ሲፀድቅ በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል ይህን የሚያስፈፅም “የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ማስተግበሪያ ፅህፈት ቤት” ተደራጅቶ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ ከነዚህ ተግባራት መካከል የተለያዩ መመሪያዎች እና የስልጠና ሰነዶች ዝግጅት እንደሚገኝበት አቶ በላይሁን ይርጋ ገልፀዋል፡፡

የፍኖተ ካርታው ዝግጅትም በፅህፈት ቤቱ አስተባባሪነት የአውሮፓ ሕበረት ባደረገው ድጋፍ በተቀጠሩ ባለሙያዎች አማካኝት የሚከናወን መሆኑም በገለጻው ተመላክቷል፡፡