የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ጋር በክልሉ በቀጣይ የፍትህ ስርዓቱን ማሻሻል እና ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ ምክክር አድርገዋል።
በምክክሩ ወቅት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በክልሉ የፍትህ ስርዓትን ለማሻሻልና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
አያይዘዉም በክልሉ የተጀመረው የፍትህ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በክልሉ የባህላዊ የእርቅ ስርዓትን በማጠናከር ውጤታማ የሆነ የፍትህ ስርዓት ማምጣት እንደሚቻልም ዶ/ር ጌድዮን ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸዉ ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ የክልሉ መንግሥት የፍትህ ስርዓቱን ለማጠናከርና ፍትህን ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህንን ለማስጠበቅ የክልሉ መንግስት በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግሮችን ህብረተሰቡን በማወያየት ሰፊ ስራ በመስራት እየፈታ እንዳለ አመላክተዋል፡፡
አክለዉም ባህላዊ የእርቅ ስርዓት የህብረተሰብን ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር እና የፍትህን ስርዓት በማገዝ ረገድ ትልቅ አቅም እንደለውም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በፍትህ ዘርፍ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።