ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር ለጉብኝት የመጡትን የፌዴራል ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራሮች የተቀበሉት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ እና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች የተቋሙ አመራሮች ናቸው።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የተመራው የልኡካን ቡድን በፍትሕ ሚኒስቴር በመገኘት ጉብኝት ያደረገ ሲሆን በጉብኝቱ ከክቡር ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ እና የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ፉአድ ናስር እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ባለስልጣናቱ በ2015 ዓ.ም በአዲስ መልክ እድሳት ተደርጎለት የተሻለ ውብ እና ምቹ የስራ ከባቢ ሁኔታ የተፈጠረለትን የፍትሕ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ውጫዊ እና ውስጣዊ የእድሳት ስራው ክፍሎችን የጎበኙ ሲሆን ተቋሙ ታሪኩን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር በማሰብ ያስገነባው ሙዚየምም የጉብኝቱ አካል ነበር።
የሁለቱ ተቋማት አመራሮች ከጎበኟቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል ሌላኛው የሆነው የግንባታ ስራው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የኮልፌ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሲሆን በፍትሕ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በግንባታ ላይ የሚገኘው ይህ ህንጻ ግንባታው ሲጠናቀቅ ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚጠቀሙበት ስለመሆኑ ተገልጿል።
ባለሰባት ወለል የሆነው ይህ ህንፃ ነባራዊ ሁኔታ 80 በመቶ የግንባታ ስራው መጠናቀቁንና ግንባታውም በያዝነው በጀት አመት ጥር ወር ላይ አልቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ መረዳት ተችሏል፡፡