ዜና

በፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ የተመራ ቡድን የቴክኖሎጅ አጠቃቀምን ተቋማዊ ባህል እንዲሆን ለማድረግ ያለመ ጉብኝት አካሄደ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ህግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ የተመራና በዘርፉ ስር ያሉ የስራ ክፍሎችን ያካተተ ቡድን በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት በመገኘት የቴክኖሎጅ አጠቃቀምን ተቋማዊ ባህል ለማድረግ የሚያስችል የስራ ጉብኝት አካሂዷል፡፡ 

በጉብኝቱ ወቅት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ጉብኝቱ በዋናነት አላማ ያደረገዉ ስራን በአካል ተገኝቶ ከመስራት በዘለለ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቀልጣፋ የስራ ስምሪት ለመስጠትና ጊዜን ቆጣቢ የሆነ የአሰራር ስርአትን መዘርጋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ልምድ መዉሰድ መሆኑን ገልጸዉ በእያንዳንዱ የስራ ክፍል አመራሩና ሰራተኛዉ የሚገናኝበት ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም አዉስተዋል፡፡

አያይዘዉም በ2016 የበጀት አመት እንደ ዘርፍም ሆነ በተቋም ደረጃ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትኩረት ካደረገባቸዉ ተግባራት መካከል አንዱ የአሰራር ስርአትን ማዘመን መሆኑንና ለዚህ ተግባርም የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት በቴክኖሎጂዉ ዘርፍ የተሻሉ ባለሙያዎችን ያሰባሰበ ፅ/ቤት በመሆኑ እንደ አንድ አጋዥ ለማድረግ የመጀመሪያ ዙር የሆነ ጉብኝት  መደረጉንና ይህንን ተግባር በመደበኛነት አጠናክሮ ለማስቀጠልም የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በመፈራረም የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር በመዉሰድ ተቋማዊ ባህል ማድረግ ለማስቻልም በቀጣይ ሌሎች ዘርፎች በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ተገኝተዉ ልምድ እንደሚወስዱ የተናገሩት አቶ በላይሁን ይህ ከሆነ በኋላ የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች በጋራ እየሰሩ ለተቋሙ የሚጠቅም ስራ ይከናወናልም ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር ዲኤታዉ እንደ ተቋምም ሆነ በዘርፍ ደረጃ እስካሁን የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸዉንና በቀጣይ ይህንኑ ተግባር በማጠናከር በቀን ተቀን ስራዎች ተግባራዊ የሚደረጉበት የአሰራር ስርአቶች የሚዘረጉ ይሆናልም ብለዋል፡፡

የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ምክትል ስራ አስፈፃሚ እና ፕሮግራም ማናጀር የሆኑት ራሄል ይትባረክ በበኩላቸዉ የተቋሙን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አስመልክተዉ ማብራሪያ ሲሰጡ ለአንድ ስራ ዉጤታማነት የሰዉ ሀይል እና የስራዉ አጠቃላይ ሂደት እንዲሁም የምንጠቀማቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸዉ ተናግረዉ የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት የሚከተለዉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለስራቸዉ ዉጤታማነት ከፍ ያለ ድርሻ እንዳበረከተላቸዉ ተናግረዋል፡፡

ቀጥሎ የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አቤኔዘር ፈለቀ የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት እየተጠቀመባቸዉ ስላሉ የቴክኖሎጅዎች ዉጤቶች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለሉኡኩ ሰጥተዋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ የልኡኩ አባላትም ለተደረገላቸዉ አቀባበልና ማብራሪያ ምስጋናቸዉን አቅርበዉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ ከፍትሕ ሚኒስቴር የስራ ሁኔታ አንፃር ያላቸዉን ጥያቄዎች አንስተዉ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ወደ ፊት በማንኛዉም ስራ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡ 

ፕሮጀክት ፅ/ቤቱ የብሒራዊ ዲጅታል መታወቂያ አዋጅ 1284/2015 ከጸደቀ በኋላ ስራዉን በይፋ እየሰራና ነዋሪዎችን በተለያዩ ባንኮችና የገቢዎች ፅ/ቤቶች በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡